| 07.01.2009 | 15:00 UTC
የተለያዩ-የገና በአል እየተከበረ ነዉ
የዩልየስን የዘመን ቀመር የሚከተለዉ በተለይም የኦርቶዶክስ ክርስትናን አማኙ አለም ዛሬ የገና በአልን እያከበረ ነዉ።በአሉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በየአመቱ እንደሚሆነዉ ሁሉ በከፍተኛ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት ተከብሯል።ከኢትዮጵያ ሌላ ሩሲያ፥ ሰርቢያና ግሪክን በመሳሳሉት ሐገራትም ተከብሮ ዉሏል።
ናይሮቢ፥አዲስ አበባ፥-የኢትዮጵያ መያድ ሕግና ተቃዉሞዉ
የኢትዮጵያ መንግሥት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ሥራ እና አሰራር የሚገድብ ሕግ በመደንገጉ ከፍተኛ ተቃዉሞና ወቀሳ እየተሰነዘረበት ነዉ።የተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባፀደቀዉ ሕግ መሠረት የዉጪ ድርጅቶች በሰብአዊ መብት፣ በፆታ እኩልነት፥በሕፃናትና በአከለ-ድኩማን መብቶች፥ በግጭት ማስወገድ እና በፍትሕ መስኮች እንዳይሰሩ ታግደዋል።ከበጀታቸዉ አስር ከመቶ እና ከዚያ በላይ የዉጪ እርዳታ የሚያገኙ የሐገር ዉስጥ ድርጅቶችም ተመሳሳይ ገደብ ተጥሎባቸዋል።የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና መያዶች ሕጉን አጥብቀዉ ነቅፈዉታል። የጀርመኑ ዜና ወኪል ዴ ፔ አ እንደዘገበዉ አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል ሕጉ የሰብአዊ መብት ጥሰትን ለመደበቅ፥ ትችትን ለማራቅ፥ እና በሁለት ሺሕ ሁለት ሊደረግ ከታቀደዉ ምርጫ በፊት የሚነሳ የሕዝብ ተቃዉሞን ለማገድ ያለመ በማለት አጣጥሎ ነቅፎታል።ኢትዮጵያ ከፍተኛ ርዳታ ከሚያገኙ የአለም ሐገራት አንዷ ናት።ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ የተለያዩ መንግሥታት ሕጉ እንዲሻሻል ጠይቀዉ ነበር።ብዙም ለዉጥ አልታየም።
እየሩሳሌም-እስራኤል ድብደባዉን ላጭር ጊዜ አቋረጠች
እስራኤል የፍልስጤምን ግዛት ጋዛ ሰርጥን መደብደቧን ላጭር ጊዜ ማቋረጧን አስታወቀች።አንድ የእስራኤል ጦር ሐይል ቃል አቀባይ ዛሬ እንዳስታወቀዉ ጦሩ ድብደባዉን ያቋረጠዉ በድብደባዉ ለተጎዳዉ ሕዝብ ሰብአዊ እርዳታ እንዲደረስ በማሰብ ነዉ።የእስራኤል ጦር ላለፉት አስራ ሁለት ቀናት የጋዛ ሰርጥን ካየር፥ ከምድርና ከባሕር ያላማቋረጥ ሲቀጠቅጥ ነዉ-የከረመዉ።በድብደባዉ ከስድስት መቶ በላይ ፍልስጤማዉያን ተገድለዋል።ሁለት ሺሕ ስምንት መቶ ቆስለዋል።የጋዛ ሰርጥ ትልላልቅ ከተሞች ከነመሰረተ-ልማት አዉታሮቻቸዉ ጋይተዋል።የእስራኤል ጦር ትናንት ብቻ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅጥር ግቢንና ድርጅቱ የሚያስተዳደርዉን ትምሕርት ቤት ደብድቦ በየቅጥር ግቢዉ ተጠልለዉ የነበረዉ አራባ-ሰወስት ሰዎች ገድሏል።በጋዛ የአለም አቀፉ ድርጅት ተጠሪ ጆን ጊንግ ለጥፋቱ ተጠያቂ መኖር አለበት ብለዉ ነበር።
«ለተወሰደዉና ላልተወሰደዉ እርምጃ ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል።የሐዘናችን ተካፋይነት መግለጫ ቃላት ከእንግዲሕ አንፈልግንም።ሁሉም ምሥል አለን።ማንም የተፈፀመዉን በትክክል መገንዘብ፥ በትክክል ማወቅ ይችላል።እንዲቆም ነዉ የምንፈልገዉ።አሁኑኑ እንዲቆም።»
የእስራኤል ጦር ለወደፊቱም ድብደባዉን በየቀኑ ለየሰወስት ሰአቱ እንደሚያቆም አስታዉቋል።የግብፅና የፈረንሳይ መሪዎች ሐማስና እስራኤል ተኩስ እንዲያቆሙ ያቀረቡትን ሐሳብ እስራኤል ከቅድመ ግዴታ ጋር እንደምትቀበለዉ አስታዉቃለች።አንድ የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ እንዳስታወቀዉ ሐማስ ተኩስ ካቆመ የእስራኤል ጦርም ተመሳሳዩን ያደርጋል።።ሐሳቡ የእስራኤል ጦር ከጋዛ እንዲወጣም የሚጠይቅም ነዉ።አካባቢዉን የጎበኙት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳት ኒካላ ሰርኮዚ ሁለቱ ወገኖች የተኩስ አቁም ሐሳቡን እንዲቀበሉት አደራ ብለዉ ነበር።
«የእስራኤል መንግሥት ጦሩ ከጋዛ ሰርጥ እንዲወጣ ጭምር ለቀረበዉ ጥያቄ ቀና ምላሽ ይሰጣል የሚል ትልቅ ተስፋ አለኝ።ይሕ ማለት ተስፋ የማደርገዉ ተኩስ እንዲቆም ብቻ ሳይሆን የእራኤል ወታደሮች እንዲወጡም ጭምር ነዉ።»
ዩናይትድ ስቴትስ ግን የእስራኤልን እርምጃ አሁንም እንደደገፈችዉ ነዉ።ከሁለት ሳምንት በሕዋላ ከሥልጣናቸዉ የሚሰናበቱት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ኮንዳሊሳ ራይስ እሳራኤል የፈፀመችዉን ጥቃት እኛም ብንሆን እንፈፅመዉ ነበር ብለዋል።
«በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ እስራኤላዉያን የሚኖሩት በየቀኑ በሮኬት ጥቃት ጥቃት አየተሸማቀቁ ነዉ።እና እዉነቱን ለመናገር ማንኛዉም ሐገር የማናችንም ሐገር እንዲሕ አይነቱን ሁኔታ ሊታገሱት አይችሉትም ነበር።»
ይሕ በንዲሕ እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት አባል ሐገራት ተወካዮች ጋዛ ሥላለዉ የሰብአዊ መብት ሁኔታ ለመነጋገር የፊታችን አርብ አስቸኳይ ጉባኤ ይቀመጣሉ።ከአርባ-ሰባቱ የምክር ቤቱ አባላት ሁለት ሰወስተኛዉ አስቸኳይ ጉባኤዉ እንዲጠራ ጠይቀዋል።ምክር ቤቱ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር በ2006 ከተመሰረተ ወዲሕ በተቆጠረዉ ሁለት አመት ከመንፈቅ እስራኤልን የሚያወግዝ ሰወስት ዉሳኔዎችን አሳልፏል።ዩናይትድ ስቴትስ አለም አቀፉን ድርጅት ላንድ ወገን የሚያዳላ በማለት አዉግዛዋለች።
መቅዲሾ-የዩጋንዳ ወታደርና የመያድ ሰራተኛ ተገደለ
ሶማሊያ ዉስጥ በደቡባዊ ጌዶ ግዛት ይሰራ የነበረ አንድ የአለም ምግብ ድርጅት ባልደረባ ማንነታቸዉ ባልታወቀ ታጣቂዎች ተገደ።የአይን ምስክሮች እንዳሉት ጭምብል ያጠለቁ ሰወስት ታጣቂዎች ኢብራሒም ሑሴይን ዱሌን እንዲቆም አዘዙት።ወዲያዉ ጥይት አረከፈከፉበት።አለም አቀፉ የርዳታ ድርጅት ግድያዉን አጥብቆ አዉግዞታል።ሶማሊያ ዉስጥ ካለፈዉ ነሐሴ ወዲሕ ሰወስት የድርጅቱ ሠራተኞች ተገድለዋል።ርዕሠ-ከተማ መቅዲሾ ደግሞ መንገድ ዳር በተቀበረ ፈንጂ አንድ የዩጋንዳ ወታደር ሲገደል ሌላ ባልደረባዉ ቆስሏል።በሌላ ዜና የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንዴዎች አግተዋት የነበረች አንዲት የቱርክ መርከብን ለቀዋል።አንዳድ የዜና ምንጮች እንደዘገቡት መርከቢቱ የተለቀቀቸዉ የመርከቢቱ ኩባንያ ለጋቾቹ ቤዛ ሥለከፈላቸዉ ነዉ።ኩባንያዉ ግን ዘገባዉን አላረጋገጠም። የቻይና የባሕር ላይ ወንበዴዎች እንዲወጋ ከዘመተችዉ ጦር የመጀመሪያ የባሕር ሐይል ጓድ ትናንት አደን ባሕረ-ሠላጤ ደርሷል።
ኪየቭ፧ ቡዳፔሽት-የሩሲያ ጋዝ ተቋረጠ
ሩሲያ ለዩክሬንና በዩክሬን በኩል ወደ ሌሎች የአዉሮጳ ሐገራት ጋዝ የሚተላለፍበትን ቧምቧ ዘጋች። የሩሲያ የነዳጅና የጋዝ ኩባንያ ጋዝፕሮም እንደሚለዉ ቧንቧዉ የተዘጋዉ ዩክሬን ያለባትን ሁለት ቢሊዮን ዶላር የጋዝ ዕዳ አልከፍልም በማለቷ ነዉ።የድርጅቱ ምክትል ሐላፊ አሌክዛንደር ሜድቬዴቭ ከዚሕም እልፍ ብለዉ ዩክሬን ጋዛችንን ሰርቃለች ይላሉ።
«እኛ እርምጃዉን የወስድነዉ በዩክሬን አማካይነት የተሰረቀብን ጋዝ ለማስመለስ ነዉ።ሌሎች የአዉሮጳ ሐገራትን እንዳይጎዱ ብንፈልግም በተጨባጭ ግን ማድረግ አልቻልም።በዚሕም ምክንያት ከፍላጎታችን ዉጪ የሆነ ዉጤት አስከትሏል።«
ዩክሬን በበኩሏ ሩሲያን ተጠያቂ ታደርጋለች።የቧምቧዉ መዘጋቱ ከዩክሬን ሌላ ሐንጋሪ፥ ቡልጋሪያ፥ ሮማኒያ እና ሶላቫኪያን ጨምሮ አስራ-ሁለት የምሥራቅ አዉሮጳ ሐገራትን ለማሞቂያ፥ ለማብሰያና ለማምረቻ ችግር አጋጥሟቸዋል።ጀርመንን ጨምሮ ወደ ሌሎች የአዉሮጳ ሐገራት የሚወርደዉ የጋዝ መጠንም ቀንሷል።የዘንድሮዉ የአዉሮጳ ክረምት ከብዙ አመት ወዲሕ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ቀዝቃዛ ነዉ።የወቅቱን የአዉሮጳ ሕብረት የፕሬዝዳትነት ሥልጣን የያዘችዉ የቼክ ሪፐብሊክ የአዉሮጳ ጉዳይ ሚንስትር አሌክዛንደር ፎንድራ እንደሚሉት ዉዝግቡ ከቀጠለ አዉሮጳ ከዚሕ ቀደም ከነበረዉ የባሳ ችግር ይገጥማታል።
«ሁኔታዉ ባለበት ከቀጠለ ከጥቂት ቀናት በሕዋላ በተለይ የባልካን አካበቢ ሐገራት ከፍተኛ ችግር ይገጥማቸዋል።የዘንድሮዉ ችግር የዛሬ ሰወስት አመት ተመሳሳይ ዉዝግብ በነበረበት ወቅት ደረሶ ከነበረዉ ችግር የጠና ነዉ።»
የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት ከአጠቃላይ የጋዝ ፍጆታቸዉ አንድ አራተኛዉ ከሩሲያ የሚመጣ ነዉ።ከሩሲያ ከሚመጣዉ ጋዝ 80 በመቶዉ የሚያልፈዉ ደግሞ በዩክሬን በኩል ነዉ።




